የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው መልካም ፍቃደኝነትና ተነሳሽነት የልፋታቸውን ዋጋ ሳይጠይቁ ወይም ከድርጊታቸው በስተጀርባ ሌላ አጀንዳ ሳይጠነስሱ በአብዛኛው ጊዜ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሰብአዊ ተግባር ነው፡፡
በዓለማችን በተለያዩ አገራት የበጎ ፍቃደኝነት ተግባር የሚያከናውኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በርካታ ናቸው። በኢትዮጵያም ዜጎች በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ከሆነ ወዲህ ዜጎች በበርካታ ዘርፎች ላይ የተለያዩ የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በግልና በቡድን የተደራጁ ግለሰቦችም አረጋውያንን፣ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን፣ ልዩ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተጎዱ ሴቶችንና ህፃናትን ያለምንም የልፋት ዋጋ (በገንዘብ የሚተመን ክፍያ ሳይደረግላቸው እና እነሱም “ይከፈለን” ብለው ሳይጠይቁ) ሙሉ ወይም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ሲያግዙና ሲረዱ ይስተዋላል፡፡
ውድ አንባቢያን፣ የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት መግለጫው ብዙ ቢሆንም ዛሬ የክረምት በጎ ፍቃደኝነት አገልግሎትን በተመለከተ ትንሽ ነገር ማለት ወደድኩ፡፡ የክረምት ወቅት ለአብዛኛው የአገራችን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ነው፡፡ ግማሹ ዘመድ በመጠየቅ፣ ግማሹ ደግሞ በትምህርት ተጨናንቆ የነበረውን አዕምሮ ዘና ለማድረግ በጉጉት የሚጠብቀው ወቅት ነው፡፡
ለአንዳንድ የአገራችን ወጣቶች ደግሞ የክረምት ወቅት ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ተግባር ለመፈፀም በበጎ ስራ ላይ በመሰማራት ሲታትሩ የሚስተዋልበት ነው፡፡
በርካታ ወጣቶች የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካኝነት ጊዜያቸውን ለሌሎች ሲሰጡና ወገኖቻቸውን በሚጠቅም ተግባር ላይ ሲያውሉ በዚያው ልክ ደግሞ በሀገራቸው ዕድገት ላይ ገንቢ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ማየት አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል፡፡
በዘንድሮ የክረምት ጊዜያትም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በበጎ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የችግኝ ተከላ በማካሄድ፣ የደም ልገሳ ንቅናቄ በማዘጋጀትና ራሳቸውም ደም በመለገስ፣ ሌሎችንም ደም እንዲለግሱ በመቀስቀስ የወገናቸውን ህይወት ማዳን እንደሚቻል አሳይተው አኩሪ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡
በከተማችን ዓለም ገበያም የደካሞችን ቤት በመገንባትና በማደስ፣ የትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ በችግኝ ተከላ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በርካታ ናቸው፡፡
አሁን አሁን ደግሞ ሀገራችን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተከትሎ፣ ክረምት ሲመጣ አብዛኛው ወጣትና በርካታ የህብረተሰባችን ክፍሎች ተረባርበው የሚፈፅሙት የችግኝ ተከላ ተግባር የማይረሳ ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡
ሁሉም ከአቅራቢያቸው በመንግስት ከተከለሉ ቦታዎች ላይ በንቅናቄ መልኩ ችግኝ በመትከል የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ሲያለመልሙ ይስተዋላል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ዛሬም መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ያደጉ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ብልፅግና ያበቃቸው የእድገት ሂደት በከባቢ አየር ላይ ያደረሰው ጉዳት በተለይም በእድገት ወደኋላ ያሉ ሀገራትን ተጎጂ አድርጓል።
ይህንን በሰው ልጆች ላይ የተደቀነ አስከፊ አደጋ ለመታገል የተለያዩ ሀገራትና ህዝቦች የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ በትጋት እየተነሱ ናቸው።
ሀገራችን እ.አ.አ. በ2011 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችላት ስትራቴጂ ቀይሳ ለተግባራዊነቱ በንቃት መረባረብ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችላለች። ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን በመወከል በጥልቅ እውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፃቸውን በዓለም መድረኮች ላይ ከፍ አድርገው አሰምተዋል፤ በተለይም የበለፀጉ አገራት በፈፀሙት የካርቦን ልቀት ያልጠፉት ታዳጊ አገራት ሊገጡ አይገባም፤ እንዲሁም ካሳ ነው የሚገባቸው በማለት ተከራክረዋል።
በአገራችንም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር የራሳችንን የቤት ስራ መስራት ይገባናል በሚል በተደረገው እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት ከጫፍ እስከ ጫፍ ህዝባችንን በማነቃነቅ ተጨባጭ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችላል። የተመናመኑ ደኖች ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል፤ የደን ሽፋናችንም እየተሻሻለ መምጣት ችሏል።
የኃይል አማራጮቻችን ከብክለት ነፃ ከሆኑ እንደ ውሃ፣ ንፋስ፣ የፀሃይ ብርሃንና እንፋሎት ከመሳሰሉት ምንጮች መሆኑ ሲታይ ደግሞ ሀገራችን በአጀንዳው ላይ ያላት ቁርጠኝነት የሰው ልጆችን በመታደግ በኩል ምን ያህል ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች እንዳለች ለመረዳት አያዳግትም።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል። ይህንን ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ደግሞ ተግዳሮቶቿን ከስር ከስር መፍታት ግድ ይላል። በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና ነውና፣ ይህም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ መቀጠሉ ስለማይቀር የአየር ንብረት ለውጥና መዛዘ ደግሞ አንዱና ዋነኛው የእድገታችን ማነቆና ስጋት ነው።
የግብርና ልማት ስራችን ባሰብነው ልክ የእድገታችን ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ካስፈለገ የመሬት መሸርሸርን በመከላከልና የደን ልማታችንን በማፋጠን የአየር ንብረት ለውጡን ግንባር ተጠቂ እንዳንሆን መስራት ያስፈልጋል።
ለዚህም ነው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከእድገታችን ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ በቁርጠኝነት መረባረብ አለብን የምንለው። የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና አለው።
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰብን ለማስቀጠልና በእርሳቸው ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀረፀውን ለአረንጓዴ ልማት የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ግብ ለማሳካት እየታተሩ ይገኛሉ።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት በሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግል ላይ የማይፋቅ የራስን አሻራ ማኖር ነውና፣ በዋጋ የማይተመን የመንፈስ እርካታንም ያጎናፅፋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዚህ በተሻለ መልኩ መጎልበትና ባህል ሊሆን የሚገባ መልካም ተግባር ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ አሁን የጀመራቸውን መልካም ተግባራት ይዞ ለበለጠ ውጤትና ተጠቃሚነት መቀጠል ይገባዋል። ይህ መልዕክታችን ነው።
 

ከስልጠና እስከ ስራ ስምሪት…….

ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ ዜጋን ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በሚሰራው ሥራ በየአካባቢው ያሉ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡እነዚህ የትምህርት ተቋማት ሰልጣኞችን በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠት ሥራ ፈጣሪ የሆነ ዜጋን በማፍራት ውጤታማ ሥራን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን በማሰልጠን በተለያየ የሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ራሳቸውን መጠቀምና ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፉበትን ዕድል እንዲፈጠርላቸው ከማድረግም በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስልጠና ዓይነት ሆኖ የመጣው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ላይም የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ሰልጣኞችን እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡
 
በዓለም ገበያ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሳንኩራ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ደግሞ ከእነዚህ ኮሌጆች አንዱ ነው፡፡ኮሌጁ ለሰልጣኞቹ ስልጠና ከመስጠት አንስቶ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እስከማድረግ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ እያበረከተ ስላለው አስተዋፅዖ፣ ሰልጣኞችን፣ አሰልጣኞችን፣ የኮሌጁን አመራር አካላትን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግረን ያሰናዳነውን መሰናዳት ከዚህ በታች ባለው መልኩ ለንባብ አብቅተነዋል፡፡ መልካም ንባብ።
የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን በማሰልጠን በየዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ከስልጠና እስከ ሥራ ስምሪት በማሰልጠን በየዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም ዜጎች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ዕውቀትና ክህሎት ከማስጨበጥ ባለፈ፣ ሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠናቸውን ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የመደገፍ ሥራ ይሰራሉ፡፡
የሳንኩራ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በ2008 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በዓለም ገበያ ከተማ አስተዳደርና በሳንኩራ ወረዳ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን በኮሌጁ በተለያየ የሙያ መስክ እንዲሰለጥኑ በማድረግ ስልጠናቸውን አጠናቀው ብቁና ተወዳዳሪ ሲሆኑ በየሙያ መስካቸው ተሰማርተው ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
ኮሌጁ በእስካሁኑ የስልጠና ሂደት 199 ሰልጣኞችን በደረጃ-2 እና በደረጃ-4 ያስመረቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በዘጠኝ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ሙስጠፋ ሸምሰዲን ነግረውናል፡፡ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች የአጭር ጊዜ ስልጠና በኮሌጁ እንዲወስዱ ከተደረገ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰልጣኝ ኮሌጁ እየተቀበለ መሆኑን ነው አቶ ሙስጠፋ የገለጹት፡፡
የኮላጁ ዲን አያያዙም፤ ኮላጁ ወደ ውጭ ሀገር ስራ ለሚሰማሩ ዜጎች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት ከጀመረበት የካቲት 2017 ዓ.ም ጀምሮ 2050 ሰልጣኞችን በመመዝገብ 1750 ሰልጣኞች ስልጠናቸውን በብቃት በማጠናቀቅ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው ሰርተፊኬት መቀበላቸውን አስረድተዋል፡፡
የኮላጁን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ የግብርና ስራን ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ሙስጠፋ ገልፀው፤ በአሁኑ ሰዓትም በሶስት የተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ሰልጣኞችንና አሰልጣኞቻቸውን በማህበር በማደራጀት ለሰልጣኞች የስራ ዕድል መፍጠር ከመቻሉም ባለፈ የኮላጁን የውስጥ ገቢ የማሳደግ ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ኢኒሺዬቲቭን ተግባራዊ ለማድረግ በእንጨትና ብረታብረት ስራ፣ በሞተር ጥገናና በወተት አቅርቦት ዘርፍ ሶስት ማህበራትን በማደራጀትና ከኮላጁ የውስጥ ገቢ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ በማበደር ሰልጣኞችን ከማሰልጠን ባለፈ ወደ ስራም የማሰማራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዲኑ ገልፀዋል፡፡የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከንዴፈ ሀሳብ ባለፈ በተግባር ልምምድ የበቁ ሰልጣኞችን ማፍራት ዋነኛ ተልዕኮአቸው እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንፃርስ “ምን እየተሰራ ነው?” ብለን ለአቶ ሙስጠፋ ያነሳነውን ጥያቄ እንዲህ ብለው መልሰዋል፡፡
“እያንዳንዱ አሰልጣኝ ለተግባር ልምምድ የሚያስፈልገውን ግብዓት አቅርቦ ኮላጁ ያለውን በጀት ታሳቢ ያደረገ የግብዓት አቅርቦት ስራ ይሰራል፤ ከዚህ በተጨማሪም በከተማው ከሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ጋር የትብብር ስልጠና የግብ ስምምነት በመፈራረም ሰልጣኞቻችን በአካባቢው ባሉ ኢንተርፕራይዞች የተግባር ስልጠናቸውን እንዲወስዱ እያደረግን ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡እኛም በሳንኩራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮላጅ የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያሰናዳነውን መሰናዳት በዚሁ እንደምንያብቃ እንገልጻለን፡፡
ሰላም!

 

Get 30% off your first purchase

X
Scroll to Top