በከተማ አስተዳደሩ ለሚተገበረዉ የኮሪደር ልማት በተዘጋጀዉ ዲዛይን ዙሪያ ዉይይት ተካሄደ!By alem / February 14, 2026 ዓ/ገበያ፣ የካቲት 07/2018 (ዓገከመኮ)በስልጤ ዞን ዓለም ገበያ ከተማ አስተዳደር በከተማዉ ዋናዉን አስፓልት ተከትሎ በሁለቱም አቅጣጫ ለሚሰራዉ የኮሪደር ልማት በተዘጋጀዉ ዲዛይን ዙሪያ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የዉይይት መድረክ ተካሂዷል።በስልጤ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የተዘጋጀዉን ዲዛይን የመምሪያዉ ምክትል ኃላፊና የፕላን ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኑረዲን መሀመድ አቅርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎበታል።የዉይይቱ ዋና ዓላማ በዲዛይኑ የተቀመጠውን እና መሬት ላይ ያለዉን ተጨባጭ ገፅታ በማየት ችግር ያለባቸዉን ቦታዎች በመለየት በቀጣይ ግልፅ በሆነ መልኩ ለመተግበር ያለመ ስለመሆኑ ነዉ የተገለጸው።መድረኩን የመሩት የዓለም ገበያ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ረሻድ ሀሰን እንደገለፁት በዚህ ወቅት የከተማዉ ማህበረሰብ በከተማዉ ልማት ያለዉ ተሳትፎና መነቃቃት የተሻለ እንደሆነና ይህንኑ ወደ ዉጤት ለመቀየር ደግሞ ፈጥኖ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።ከወሰን ማስከበር እና ዲዛይኑን መሬት ላይ ከማዉረድ ጀምሮ ያሉ ተግባራትን በልዩ ትኩረት መምራትና ማሳለጥ እንደሚያስፈልግም ነዉ አቶ ረሻድ የተናገሩት።ከምንም በላይ የአመራሩ እና ዘርፉን የሚመሩ ባለሙያዎች ቁርጠኝነት ፣ ቅንጅት እና የጋራ መናበብ ለተግባሩ መሳለጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዉ ተግባሩን ከምንም በላይ በፍጥነት እና በጥራት ለመስራትና ይበልጥ ዉጤታማ ለማድረግ ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።በበጀት ዓመቱ ሙሉ በመሉ ወደ ስራ ለመግባትና ከተማችንን ዉብ እና ማራኪ ለማድረግ የተዘጋጀዉ የኮሪደር ልማት ዲዛይን የእግረኛ፣ የሳይክል የግሪን ኤሪያ እና የኤሌክትሪክና የውሃ መስመርን ያካተተ በመሆኑ ለከተማችን የሚመጥን ሆኖ መገኘታቸው ተናግረው በኮሪደር ልማት መካተት ያለባቸው ስራዎች በዲዛይኑ ላይ በመጨመር በድጋሚ አጠቃላይ የከተማው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይተቻል በማለት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።በዉይይቱ በተሻሻለው ዲዛይን መነሻ አመራሩና ባለሙያዎች በጥልቀት በማየት እና ሀሳብ በመለዋወጥ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ዉይይቱ ተጠናቋል::